የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሃሳብ ለፌዴራል ተቋማት የመንግሥት ሠራተኞች የተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ
__
(ኀዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም.አዲስ አበባ): የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች እና ሠራተኞች “የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሃሳብ ለፌደራል ተቋማት የመንግሥት ሠራተኞች በተዘጋጀ መነሻ ጽሑፍ ላይ ውይይት አካሂደዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው እንደ ሕዝብ የምናልመውን መልካም ተስፋ በተግባራዊ ሥራ መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኛ ለአገር ተጨማሪ ዕድገት የሚያመጡ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለማከናወን የላቀ ሞያዊ ብቃት በመላበስ ለተግባራዊነታቸው በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን በመሆኗ በመንግሥት በኩል ለአገር ዕድገት የተቀመጡ የለውጥ ሕልሞች በዲፕሎማሲው ዘርፍ እውን ይሆኑ ዘንድ በትጋት እና በሕብረብሔራዊነት መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

በአገሪቱ እየተደረጉ ያሉ የለውጥ ሥራዎችን በተገቢው በመረዳት እና ከከፋፋይ ትርክት በመውጣት ለአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት መጣር እንደሚገባ አንስተዋል።

የውይይት መነሻ ጽሑፉን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ አቅርበዋል።

እርሳቸው በጽሑፋቸው እንደ አገር ባለፉት አምስት ዓመታት በሁለንተናዊ ዘርፎች የተደረጉ ለውጦች እና ያስገኟቸውን ውጤቶች አብራርተዋል።

በቀረበው መነሻ ጽሑፍ ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄ እና አስተያዬት ቀርቦ ከመድረክ በተሰጠ ምላሽ እና ማብራሪያ ውይይቱ  ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *