የሱዳን ቀውስ እና ቀጠናዊ ተጸእኖ አንድምታ ለኢትዮጵያ የሚል የፖሊሲ ምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከብሄራዊ ደህንነት ዮኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የሱዳን ቀውስ እና ቀጠናዊ ተጸእኖ፡ አንድምታ ለኢትዮጵያ በሚል ርዕስ በብሔራዊ ደኀንነት ዮኒቨርስቲ የፖሊሲ ምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
በምክክር መድረኩ በመገኘት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ጃፋር በድሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም የአፍሪካ ቀንድ አሁን ላይ ውስብስብ የሆኑ መልከ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች ላይ እንደሚገኝ ገልታ ከነዚህም ሁነቶች መካከል በጎረቤት ሀገር ሱዳን የተከሰተው ጦርነት በሁለቱ ወገኖች መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት በሱዳን እና ህዝቧ ላይ ካስከተለው ጉዳት አልፎ በአጎራባች ሃገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሱዳን ተፈናቃዮችን ከማስተናደግ ባለፈ በጎረቤት አገራት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ኢኮኖሚያዊ፣ የደህንነት እና ማህበራዊ ተጽእኖ እያደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የተከበሩ አቶ ጃፋር ኢትዮጵያም እንደ አንድ ጎረቤትና ከሱዳን ጋር የታሪክና የህዝብ ትስስር እንዳላት አገር ይህ ጦርነት ቀጥተኛ ተጸእኖ ከሚያርፍባቸው አገራት አንዷ መሆኗ እሙን መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
አክለውም ዋና ዳይሬክተሩ የጎረቤት ሃገራት ሰላም ኢትዮጵያ ለጀመረቻቸው የሰላም ፣የድፕሎማሲ እና የዲሞክራሲ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ጭምር መሆኑን አስገንዝበው ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በወንድማማችነት መንፈስ የሚደረገው ድጋፍ የጎላ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ም/ ዋና ዳይሬክተር እና የጥናትና ምርምር ኃላፊ የሆኑት የተከበሩ ዶ/ር አብዲ ዘነብ በበኩላቸው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከሰሜን ከማዕከላዊ አፍሪካ ጋር ጭምር የምትጎራበት ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላት በመሆኑ ኢትዮጵያ ለቀውሱ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ከእነዚህ ሃገራት ጋር መስራት እንደሚጠበቅባት አመላክተው በጦርነቱ ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ድጋፍ በሰላሙም ለመድገም ጥረቱን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ገልጸዋል፡፡
በፖሊሲ ምክክር መድረኩ ጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት፣ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ፣ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ ዲያስፖራ አገልግሎት እንዲሁም ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
የመረጃ ምንጭ ኢቢሲ
