እንደሚታወቀው የሰው ልጅ እንስሳትን ለምግብነት፣ ለመጓጓዣ፣ ለመዝናኛነት፣ ለቱሪዝም፣ ለእርሻ ስራ፣ መድሀኒት ለማዘጋጀት፣ ለስፖርትና እና ለመሳሰሉት በርካታ ጉዳዮች ይጠቀሟቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቆዳቸውን፣ ጥርሳቸውን፣ ጸጉራቸውን እና ላባቸውን ለልብስና ጌጣጌጥ ለመስራት ይውላሉ፡፡ ከዚህ ወጣ ባለ መልኩም እንስሳት የሰዎችን ባህሪያት መግለጫም ናቸው፡፡ ተንኮለኛ የሆነን ሰው እባብ፤ የዋሁን በግ፤ ንቁ የሆነውን ቆቅ፡ ጉልበተኛውን አንበሳ እና ወዘት በማለት ይጠሩዋቸዋል፡፡ ከዚህ ከተለመደውና ከሚታወቀው ውጪ እንስሳት በዲፕሎማሲ ስራ ውስጥ ሲጠቀሟቸው ይስተዋላል፡፡ የዚህም ጽሁፍ ትኩረት እንስሳትና የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚል ነው፡፡
የተለያዩ አገራት መሪዎች በተለይ በህይወት ያሉ ብርቅዬ እንስሳትን ለጎብኚ አገር መሪ ስጦታ በመስጠት የዲፕሎማሲ ስራዎችን ሲያከናውኑ ይስተዋላል፡፡ ይህንን አይነት ዲፕሎማሲ አንዳንዶቹ የእንስሳት ዲፕሎማሲ (Animal Diplomacy) በማለት ይጠሩታል፡፡ ለአብነት ያክል ቻይና የአገሯን ብርቅዬ እንስሳ የሆነውን ፓንዳ የሚባል እንስሳዋን ለጎብኚ አገር መሪ በመስጠት ወይም ለተወሰነ ጊዜ በማዋስ ትታወቃለች፡፡ ይህንንም ተግባር የፓንዳ ዲፕሎማሲ በማለት ሰይማዋለች፡፡ በተመሳሳይም አውስትራልያ የካንጋሮ ዲፕሎማሲ፣ ማሌዥያ ኦራንግተን ዲፕሎማሲ(Orangutan Diplomacy) የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ ህንድም እንደቤት እንስሳ የምትጠቀምበትን ዝሆን ከሀያ በላይ ለሚሆኑ ለጎብኚ አገር መሪዎች በስጦታ ሰጥታለች፡፡
የአገር መሪዎች እንስሳትን ለጎብኚ መሪዎች የሚሰጡበት ምክንያት በርካታ ቢሆንም በዋናነት የወዳጅነት መግለጫ ለማድረግ፤ የብርቅዬ እንስሳት መኖርን ለማሳየትና ቱሪዝምን ለመሳብ፣ የፖለቲካ ውጥረት በማርገብ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማጠናከር እና የመሳሰሉት ዓላማዎች አሉት፡፡ ይህንን መሰል የእንስሳት ስጦታ ከጥንት ጀምሮ ሲከናወን እንደነበር ታሪክ ያሳየናል፡፡ በተለይ ታንግ ስርወ መንግስት በነበረበት ዘመን (618-907) የቻይና ንጉሶች እንስሳትን ለስጦታነት ይጠቀሟቸው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በጥንት ጊዜ ተፈጥሮን ተቆጣጥረናል የሚል መልእክት ለማስተላለፍም አገሮች የአንበሳ፤ ነብር እና የመሳሰሉትን ስጦታ ይሰጡ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በንግስተ ሳባ እና የሰለሞን አፈታሪክ ውስጥም እንደተጠቀሰው ንግስት ሳባ ለንጉሱ በርካታ ስጦታዎችን ይዛ የሄደችው በግመል አስጭና እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ የሚያሳየው እንስሳት በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ውስጥ እንደሚታዩና አሁንም በአለው ዘመን መቀጠሉን እንረዳለን፡፡

ከዚህ ወጣ ባለ መልኩም እንስሳት በመሪዎች ስብሰባ ላይ ሲከሰቱ ተስተውሏል፡፡ በአስገራሚነቱ የሚነሳው ፕሬዝደንት ፑቲን እና የጀርመኗ አንጌላ ሜርኬል በሩስያ ውስጥ ሲገናኙ ፑቲን በጣም ትልቅ እና ጥቁር የሚያስፈራ ኮኒ የሚል ስያሜ ያለውን ውሻቸውን (Labrador dog) ይዘው መገኘታቸው ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1995 ሜርኬል በውሻ ከተነከሱ በኋላ ውሻ በጣም ነው የሚፈሩት፡፡ ይህ ወደሚወያዩበት ክፍል የገባው ትልቅ ውሻ ያልታሰረ እንደመሆኑ ወደ አንጌላ ሜርኬል ተጠግቶ እግራቸውን በማሽተትና በመዟዟር ሂደት ውስጥ ሜርኬል ተጨንቀውና እጃቸውን እግራቸው ላይ ለጥፈው በሚዲያ የተላለፈው በግርምትነት ይነሳል፡፡ በዚህ ሂደት ፑቲን አንጌላ ሜርኬል የሚያሳዩትን ድንጋጤና የስሜት መረበሽ እያዩ ፈገግ ይሉ ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ የተበሳጩት ሜርኬል ጉዳዩን በዝምታ አላለፉትም፤ በጽሁፍም ቅሬታቸውን ለፕሬዝደንት ፑቲን ገልጸዋል፡፡ ፕሬዝደንት ፑቲንም ይፋዊ መግለጫ ሲሰጡ እኔ ማርኬልን ለማስደንገጥ ሳይሆን መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሁኔታ ለመፍጠር ነበር፤ ለአመታት በጀርመን ስኖር የአገሩ ህዝብ ውሻ እንደሚወድ ስለማውቅ ማርኬልም ደስ ይላቸዋል የሚል ሀሳብ በመያዝ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ፕሬዝደንቷን ያስከፋ በመሆኑ ይቅርታ እጠይቃለሁ ብለዋል፡፡
ማሌዥያ ከፍተኛ የፓልም ዘይት አምራች እንደመሆኗ መጠን ይህንን ዘይት በብዛት ለሚገዟት አገር መሪዎች ኦራንጉታን የሚባል እንስሳ በስጦታ ትሰጣለች፡፡ ለዚህም ስጦታ መነሻዋ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን የውጭ ንግድ ግንኙነት ለማጠናከርያ እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ የእንስሳት ዲፕሎማሲ ለማከናወን የእንስሳውን አኗኗር ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባል፤ አልያ ስጦታው የተፈለገውን አላማ ላያሳካ ይችላል፡፡ ለአብነት ያክል ሩስያ አንዳንዴ ለሌሎች አገር መሪዎች እንደምታደርገው በረዶ ላይ የሚኖርን ድብ(Polar bear) ለኢራን መሪ ልስጥ ብትል በረዶ ላይ ሲኖር የነበረ እንስሳ በረሃ ላይ መኖር ስለማይችል ስጦታው ተገቢነት አይኖረውም ማለት ነው፡፡
ቻይና ለአሜሪካ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት ፓንዳ (ስማቸውም Ling-Ling and Hsing-Hsing) ስጦታ ሰጥታ የነበረበትን ሀምሳኛ አመት በ2022 አክብረውታል፡፡ ይህ ስጦታ እ.ኤ.አ በ1972 የአሜሪካኑ ፕሬዝደንት ኒክሰን ቻይናን ሲጎበኙ በማኦ ዜዱንግ የተሰጠ ስጦታ ነበር፡፡ ይህ አይነት የፓንዳ ስጦታ በተለያየ ጊዜ አሜሪካንን ለመሩት ፕሬዝደንቶች ሰጥታለች፡፡ ከዚህ በፊት የተሰጡ ሁለት ፓንዳዎች በአሜሪካን ውስጥ በመውለዳቸው የተወለደው ይመለስልኝ የሚል የቻይና ጥያቄ ብዙ ክርክሮችን አስተናግዶ ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው የአንድ አገር ብርቅዬ እንስሳት በሌላ አገር የሚራባና የሚባዛ ከሆነ ብርቅዬ መሆኑ ስለሚያበቃ በአብዛኛው ለውሰትና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንዲመለስ በሚል ስምምነት የሚሰጥ መሆኑንያሳየናል፡፡ ቻይና በውሰት የምትሰጣቸው ፓንዳዎች የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም ወይም እንዲመለሱ የሚደረገው አንዳንዴ የፖለቲካው ትኩሳት እየታየ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በስጦታ የሚሰጡ እንስሳት በህይወት ያሉ ሆኖ እንስሳዎቹ የዱር ወይም የቤት እንስሳ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንስሳት ሰው ሊተናኮሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ለአብነት ያክል የኢንዶኔዥያው መሪ ለአሜሪካ ፕሬዝደንት ቡሽ የሰጡት ስጦታ ኮሞራዶ ድራጎን የሚባልና አንድ ጥጃ መብላት የሚችል እንስሳ ነው፡፡ አሜሪካኖች በስጦታ የሚቀበሏቸውን እንስሳት ለሶስት ወራት በተለየ ቦታ በማቆየት (quarantine) እና ጤናቸውን ከአረጋገጡ በኋላ ወደ እንስሳ መሰባሰብያ (zoo) ይወስዷቸውና ይቀላቅሏቸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው የእንስሳ በሽታ ወደ ተሰባሰቡ እንስሳት በቀጥታ መቀላቀል በጥብቅ የሚገኙ ሌሎች እንስሳትን በበሽታ እንዲያዙ ስለሚያደርግና እንዳይሞቱ ነው፡፡
የእንግሊዟ ንግስት ኤልዛቤት ሁለተኛ እንስሳ የሚወዱ ስለነበር ከበርካታ አገሮች የተለያዩ የእንስሳ ስጦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለአብነት ያክል ከኬንያ እና ካሜሩን ዝሆን፤ ከላይቤርያ ጉማሬ፤ ከሲሸልስ ኤሊ ስጦታዎች ተቀብለዋል፡፡ በወቅቱ የተገኙ ብዙዎቹ እንስሳት በሎንዶን በሚገኘው የእንስሳ ማሰባሰብያ (Whipsnade Zoo) እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ ንግስቲቷ እንስሳዎቹን ሲጎበኙ ያሳለፏቸውን የጉብኝትና የስራ ወቅቶች በጥሩ መንፈስ እንዲያስቧቸው ለማድረግ ሊሆን እንደሚችልና የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡
አገሮች የእንስሳ ዲፕሎማሲን የሚጠቀሙት እንደ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አካል በማድረግና ገር ሀይልን (Soft power) ለማስፋት ነው፡፡ የእንስሳት ስጦታም እንደመልካም ምኞት መግለጫም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ሂደት ግን በስጦታ የሚሰጡ እንስሳትን ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ማዘዋወር የራሱም ችግር እንዳለው ይታያል፡፡ አንዳንድ እንስሳት አካባቢ በመቀየራቸው ምክንያት ጤናቸው የሚጓደልበትና የሚሞቱበት ገጠመኞች ብዙ ናቸው፡፡ ይህም በብረት አጥር ውስጥ (cage) ተገድበው ለበርካታ ሰአታት መጓዛቸው፤ በሌላ አገር ያለው የአየር ንብረት ለውጥ እና ከሚመስሏቸው እንስሳት መለየታቸው፤የምግብ ሁኔታና የመሳሰሉት ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገለጻል፡፡

በህይወት ያሉ እንስሳትን ለስጦታ ሲሰጥ መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያግዝ እንደሆነ ከላይ የተጠቀሰ ሲሆን፡ የእንስሳትን ውጤት ግን ብዙም ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል፡፡ በተለይ የእንስሳ መብት ተከራካሪ ወገኖች እንስሳት ባልተፈለገ መልኩ እንዲጎዱ አይፈልጉም፡፡ አንዳንድ አገራት የእንስሳትን ውጤት በስጦታነት አይቀበሉም፡፡ ለምሳሌ ያህል ከብት ብዙም የማይበሉ ህንዶች የቆዳ ውጤት የሆነ ስጦታ መቀበል አይፈልጉም፡፡ በተመሳሳይም በርካታ አገሮች ከዝሆን ጥርስ የተዘጋጁ ጌጣጌጦችን በስጦታ መልክ አይቀበሉም፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖችም ከእንጨት የተሰሩ ስጦታዎችን አይቀበሉም፡፡
ወደእኛ አገር ስንመጣ ኢትዮጵያ በርካታ ብርቅዬ እንስሳት አሏት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋልያ፤ኒያላ፤ቀይ ቀበሮ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን እንስሳት በመጠቀም የዲፕሎማሲ ስራ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ጥሩ መሆኑን የቻይና ተሞክሮ ያሳየናል፡፡ በመሆኑም “የዋልያ ዲፕሎማሲ”፣ “የኒያላ ዲፕሎማሲ” እና ወዘተ በማለት አዲስ የዲፕሎማሲ ካርድ መፍጠር ያስችላል እላለሁ፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ ካርድ በርካታ ቱሪስቶችን ለመሳብ ያግዛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሚዲያ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ ለአብነት ያክል አንድ የምእራብ አገር መሪ ወደ አገራችን ሲመጣ ብርቅዬ እንስሳ የሆነውን ዋልያ ለጥቂት ወራት ወይም አመታት በትውስት ቢሰጠውና በውጭ ሚዲያ ቢተላለፍ ይህንን የሚያዩ ቱሪስቶች እንስሳውን በአካል ለማየት ሊነሳሱ ይችላሉ፡፡ ስጦታውን ከሚቀበል አገር ጋር የሚኖረንም የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲጠናከር ወይም እንዲሻሻል የማድረግ እድል ሊፈጥር ይችላል፡፡
መላኩ ሙሉዓለም ቀ.
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስልጠና ዳይሬክተር ጄኔራልና ተመራማሪ
melakumulu@yahoo.com
