ኢትዮጵያ በቀጣና ፣በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ ሚና በማላቅ በትብብር መንፈስ እንደምትሠራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለፁ
ሚኒስትሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር በዛሬው ዕለት የስራ ገለፃና ትውውቅ አድርገዋል ።
ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሊከተላቸው የሚገቡ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ሠጥተዋል።
ለተለዋዋጭ ቀጣናዊና ዓለምአቀፍ ክስተቶች በዕውቀት እና በምርምር የታገዘ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል ።
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ዓለምአቀፍ ግንኙነት ታሪክ ባለቤት በመሆኗ በቀጣናው እና በአህጉር ደረጃ በሚኖራት ሚና እና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ ዲፕሎማሲዋን ይበልጥ በማላቅ መስራት እንደሚገባ አውስተዋል ።
በዓለምአቀፍ መድረክ ኢትዮጵያ በሚኖራት የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች የጋራ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ትብብርን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል ።
ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው የተጀመሩ የውጭ ግንኙነት የለውጥ ተግባራትን በማጠናከር ለጋራ ግብ እና ለውጥ እንደሚሠራ ተናግረዋል ።
የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች በበኩላቸው በትብብር መንፈስ ለላቀ ውጤት እንደሚሰሩ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም
