ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለውን ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የበለጠ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ
(ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም.አዲስ አበባ):- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች በ2017 ዓ.ም.የ100 ቀናት የሪፎርም እና ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈጻጸሞች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ጃፋር በዱሩ ባለፉት 100 ቀናት በተከናወኑ ሪፎርም እና ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈጻጸሞች ዙሪያ መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል።የተከበሩአቶ ጃፋር የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አመርቂ ስኬቶችን ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የተደረገው ማሻሻያ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት፣የተሻሻለ የመንግሥት ገቢና ኢንቨስትመንት ፣የቀነሰ የመንግሥት ዕዳ ጫና፣ተወዳዳሪ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ያደገ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ስኬት ተመዝግቧል።
ውይይቱን የመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው የተደረገው ማሻሻያ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከቀጣናው ከአሕጉሩ እና ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጋር የበለጠ የሚያስተሳስር ነው ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችች የበለጠ ለማስተዋወቅ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ እና አገራዊ ፈተናዎች ባሉበት ኢኮኖሚው እያደገ መሄዱ ትልቁ የማሻሻያው እርምጃው ስኬት መሆኑንም ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል።
