ባኩ አዘርባጂያን እየተካሄደ ካለው የኮፕ 29 ጉባኤ ምን እንጠብቅ?
የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለ29ኛ ጊዜ በአዘርባጃኗ ዋና ከተማ ባኩ እየተካሄደ ነው። የተ.መ.ድ. ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ በርካታ ሃገራት መሪዎቻቸውን በመላክ እየተሳተፉ ሲሆን ሃገራችን ኢትዮጵያም ክቡር ርዕሰ ብሔር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ስላሴ የሚመሩት ልዑክ ልካለች፡፡ በጉባዔው መክፈቻ ላይ የተ.መ.ድ. ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የአየር ንብረት ተፅዕኖ አስከፊ ደረጃ መድረሱን በመግለፅ ዓመቱ ከምንግዜም በላይ ሞቃታማ ዕለታት፣ ወራት እና ዓመት የነበረበት እንደሆነ ገልፀው ለችግሩ መፍትሄ ላይ የምንደርስበት ጊዜው አሁን እንደሆነ ጉባዔተኞች አበክረው አሳስበዋል።
ይህ ጉባኤ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ በዚህም ሃገራት የድርድር አጀንዳቸውን የሚሸጡበት፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታ ተሞክሮዎቻቸውን የሚያጋሩበት፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዘላቂ አጋርነት እና ትስስር የሚፈጥሩበት፤ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን የሚያሳዩበት እንዲሁም ጉዳቶቻቸውንም የሚያሳዩበት መድረክ ነው፡፡
የዘንድሮው ኮፕ 29 የሃያላን ሃገራት ዋና ዋና መሪዎች ያልታደሙበት፤ በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት እና በወቅቱ የአሜሪካ ምርጫ እና የምርጫ ውጤት አትኩሮት የተነሳ ጉባኤው ብዙም ሽፋን ያላገኘበት መሆኑን ጉዳዩን በትኩረት የሚከታተሉት ወገኖች የገለፁ ሲሆን በዚያው ልክም የዘንድሮው ጉባኤ ከሌላው ጉባኤ ሲነፃፀር የወጣቶች እና የባለ ብዙ ወገን ድርጅቶች ተሳትፎ ያየለበት ነው የሚሉ ወገኖችም አልታጡም፡፡
ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቋቋም ፍትህ ይጠይቃሉ! የጉዳት ካሳም እንዲሁ! በዘንድሮው ኮፕ 29 ጉባዔ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ጉዳይ ቁልፍና አንገብጋቢ አጀንዳ ነው። ኮፕ መካሄድ ከጀመረ 30 ዓመታት ቢያስቆጥርም የተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ግን አናሳ ነው ተብሎ ይነገርለታል፡፡ ሀገራት የሚጠበቀውን ያህል ሲተገብሩና ሲያሳኩ አይታይም፡፡ ለምሳሌ በዋና ዋና ጉዳዮች እስካሁን ውሳኔ ላይ አልተደረሰም፡፡ ውሳኔ ካልተደረሰባቸው ውስጥ የካርቦን ልቀት፤ የጉዳት ካሳ፤…ወዘተ፡፡ በኮፕ መድረኮች የተንጠለጠሉ ወይም ያልተቋጩ አያሌ ጉዳዮች፣ እልባት ያላገኙ ረቂቅ ሰነዶችና ስምምነቶች ስላሉ በዘንድሮው ጉባዔ እልባት ያገኛሉ የሚል ተስፋ ተሰንቋል። ለአብነትም የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አካል የሆነው የታዳጊ ሀገራት ጉዳት ካሳ (Loss and Damage) ጉዳይ ላይ አንድ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ይጠበቃል። በተጨማሪም መንግስታት ኢኮኖሚያቸውን ከነዳጅ ይልቅ በታዳሽ ኃይል ላይ እንዲመሰረቱ፤ የዓለም ሙቀት መጠንም ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሼስ በላይ እንዳይጨምር መገደብን ጨምሮ ሃገራት የአየር ንብረት ግቦችን የሃገራዊ ዕቅዶቻቸው አካል አድርገው እንዲሰሩ ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *