መግቢያ፤

ያለፈው ጳጉሜ ወር የኢትዮጵያዊያን የጋራ አሻራ  ውጤት የሆነው እና የአገራችንን ጂኦ-ፖለቲካዊ ቁመና ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀይረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ በይፋ የተመረቀበት ታሪካዊ ወር ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች፣ ትክክለኛ ፖሊሲ ተቀርጾ እና ቀጠናዊና አለም አቀፍ ሁኔታዎቸን በሰላ መልኩ በመጠቀም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለብዙ አገራት መትረፍ የሚችሉ ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶችን ማከናወን የሚያስችል እምቅ አቅም ያላት ናት፡፡ በኃይል ዘርፍ ብቻ ብናይ ከ60 ሺህ በላይ የታዳሽ ኃይል አቅም ያለ ሲሆን 45 ሺህ ከሃይድሮፓወር፣ 10ሺህ ከነፋስ እና 5ሺህ ከጂኦተርማል ሊገኝ የሚችል ነው፡፡ ይሁንና በተለያዩ የውስጥ እና የውጭ ተግዳሮቶች የተፈጥሮ ፀጋዎቻችንን የማልማትና የመጠቀም ሁኔታችን ደካማ ነበረ፡፡

የህዳሴው ግድብ ግንባታ በመጋቢት 2003 ዓ.ም በይፋ መጀመር ብዙ አሉታዊ ቀንበሮች መሰበር መጀመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ከንጉስ ኃ/ስላሴ ጊዜ ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ ድረስ በውጭ እርዳታና ድጋፍ በመታገዝ ኢትዮጵያዊያን አባይን ለማልማት የነበራቸው ፍላጎት በግብጽ የተቀናጀ ሴራ እና በሌሎች አጋፋሪ አገራትና ተቋማት ተጽኖ ሊሳካ አልቻለም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን የነበራቸው አማራጭ በጨለማ ቁጭ ማለትና ትልቁን ሀብታቸውን በቁዘማ መመልከት ወይም ካልሆነ ያለውን የውስጥ አቅም አሰባስቦና ጫናዎችን ለመቋቋም ዝግጁ ሆነው ቀንበር ሰባሪ እርምጃ መጀመር ነበረ፡፡ በዚህ አግባብ የግድቡ መሰረት ድንጋይ የዛሬ 14 ዓመት ሲጣል ለብዙ ኢትዮጵያዊያን የደስታና የጽናት ጉዞ ጅማሮ፣ ለተችዎችና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የስላቅ፣ የጥርጣሬ፣ የሴራ ማውጠንጠኛ ጅማሮ ነበረ፡፡

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያዊያን በጀመሩት የደስታና የእንችላለን መንፈስ በቦንድ ግዥ፣ በስጦታ፣ በቁስ እና በዕውቀት ያላቸውን ለግድቡ በማበርከት ከመንግሥት ጎን ቆመዋል፡፡ በሌላ በኩል ግብጽ በተለያዩ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም ወታደራዊ መንገዶች ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ የመክተት ስራዎችን ስታከናውን ቆይታለች፡፡

በተለይም ከ2010 ዓ.ም ከአገራዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ መሰረታዊ ማሻሻያዎች ከተደረገባቸው አንዱ የሜጋ ፕሮጀክቶች ጉዳይ ሲሆን ከእነዚህ ግንባር ቀደሙ የህዳሴው ግድብ ስራ ነው፡፡ የለውጥ መንግሥት የነበረውን የፕሮጅክት አመራር እና የሃብት አሰባሰብና አጠቃቀም ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም የነበሩ የውስጥ ክፍተቶች እንዲታረሙና የግንባታ ስራው ዳግም በተፋጠነ ሁኔታ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ በዚህ ረገድ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ጂኦ-ፖለቲካዊ ቁመና ለማስተካከል ቁልፍ ሚና እንዳለው በመረዳት ጠንካራ አመራር በመስጠትና ልዩ ክትትል በማድረግ ለዛሬ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን ተያያዥ ቀጠናዊና አለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ባለፉት ዓመታት በተሳካ ሁኔታ አከናውናለች፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀምን የሚደነግገው የመግባቢያ ስምምነት (Declaration of Principles-DoP) ተፈርሟል፡፡ ግብጽ ለአስራ ሶስት (13) ጊዜ ያህል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ ያደረገችው ፀረ-ኢትዮጵያ ጥረት ከወዳጅ አገራት ጋር በመቀናጀት እንዲከሽፍ ተደርጓል፡፡ በተከታታይ ዙሮች በተደረጉ ሶስትዮሽ እና ሌሎች ውይይቶችና ድርድሮች ኢትዮጵያዊያን ኢንጂነሮች፣ ዲፕሎማቶችና የህግ ምሁራን በተቀናጀ አኳኋን እና በሳለ ስልት በመጠቀም አገራችን ጥቅሟ እንዲከበር አድርገዋል፡፡ በግብጽ በኩል የሚቀነቀነውን የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን የሚሽረው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Cooperative Framework Agreement-CFA) እ.ኤ.አ በ2010 የተፈረመና በ2024 ገዥ ስምምነት የሆነ ሲሆን የተፋሰሱ ኮሚሽን (Nille Basin Commission-NBC) በመቋቋም ሂደት ላይ ነው፡፡

እነዚህ ቁልፍ ሁኔቶች ከግድቡ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ ጋር ተደምሮ በናይል ተፋስ አዲስ ጂኦ-ፖለቲካዊ ምህዳር መፈጠሩን እና ኢትዮጵያ አሁን የምትሰማ፣ ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶችን አቅዳ የምትፈጽም፣ ጫናዎችን በትጋት ማለፍ የምትችል መሆኗን ይመሰክራሉ፡፡ ስለሆነም ከግድቡ ግንባታና መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ የተገኘውን ታላቅ ድል በተለያዩ አግባቦች ማጉላትና ማስፋት ዘርፈ-ብዙ ፋይዳዎች አሉት፡፡

ለምን ታላቁን ስኬት ማጉላት እና ማስፋት አለብን?

ከህዳሴው ግድብ ድል ጋር በተያያዘ እንደ አገር ስኬቱን እንድናጎላና እንድናሰፋ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ እውነታዎችና ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛ ትሩፋቶቹ ትልቅ ናቸው፡፡ ህዳሴ በአገር ውስጥ የኃይል ተደራሽነትን አሁን ካለበት 55% አካባቢ ትርጉም ባለው መጠን ከፍ ያደርጋል፡፡ በተያያዘ የአገሪቱን የኃይል ሽያጭ ገቢን የሚያሳድግ ሲሆን በቀጠናው የአገሪቱን የኃይል ማዕከልነት ያረጋግጣል፡፡ እንደ አገር ህዳሴ የተሞክሮ ምንጭ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ከሀብት አሰባሰብና ከሌሎች የግድብ ስራዎች ጋር በተያያዘ የነበረው የጋራ ርብርብ እና ህብር ከተባበርን አሁንም የማንገፋው ተራራ እንደለሌ አሳይቶናል፡፡ ስለዚህ በህዳሴ ለምናስባቸው ስትራቴጂክ አገራዊ ስራዎች ስንቅ የሚሆን የይቻላል መንገድ ይዘናል፡፡ 

ሁለተኛ ስኬቱ ትልቅ ነው ግን በኃይል ዘርፍ ሆነ ህዳሴውን በሚመስል ስትራቴጂክ ስራ እንደ አገር የመንሻው፣ የሚያስፈልገን፣ አቅማችን ገና አልተነካም፡፡ እንደ አገር ካለን አጠቃላይ የውሃ ሀብት አቅም እየተጠቀምን ያለነው ከ5% ያነሰ ነው፡፡ እንደ አገርም እንደ ቀጠናም ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት እና ዕድገት ስላለ አንደ አገር መብራት ተደራሽ ማድረግና በፍጥነት እያደገ ያለውን የኢንዲሱትሪ ዘርፍ የኃይል ፍላጎት ማርካት፣ ለቀጠናው አገራት ኃይልን ተደራሽ ማድረግና ያለውን የኃይል ትስስር ከማጠናከር በተጨማሪ አዳዲስ አገራትን ማዳረስ ያስፈልጋል፡፡

ሶስተኛ ምንም እንኳን ህዳሴው ትልቅ ቀንበር ሰባሪ ድል ቢሆንም አሁንም የግብጽና ሌሎች ተጽኖ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ግብጽ በናይል ላይ ያላትን የፍላጎት-አቋም-ኃይል ጥምርታ (Interest-Position-Power Matrix) በቅርቡ የምትቀይር ወይም የሚቀየር አይመስልም፡፡ በግብጽ እና በቅርብና በሩቅ አስቻዮቿ ዘንድ ለኢትዮጵያ ሆነ በናይል ተፋሰስ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ያለው ፍላጎት የተዛባና እና በአይችሉም፣ አይገባቸውም መንፈስ የተሞላና ስር የሰደደ ነው፡፡ ግብጽ ከእኛ አንጻር አሁንም የበላይነቶች አሏት፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተፈላጊነቷ ከፍ ያለ ነው፣ የተለያዩ ቀጣናዊና አለም አቀፍ ማዕቀፎችን በመጠቀም ዲፕሎማሲያዊ ተጽኖ ለማሳደር መሞከሯ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በሱዳን ያላት ተጽኖ ቀጥሏል፣ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላምና እስራኤል ደህንነት ያላት ድርሻ አሁንም ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በህዳሴው የተገኘው ድል ኢትዮጵያ ለደረሰባት ጂኦ-ፖለቲካዊ ጭቆና መሰበር አንዱ መደላድል ቢሆንም ሙሉ ቁመና ላይ እንደማያስቀምጠን እና የግብጽ ሆነ የሌሎች አገራት የተጽኖ ኢላማ መሆናችን የሚቀጥል መሆኑን በመረዳት በተፋሰሱ ተጨማሪ ግድቦችን መግንባት፣ አገራዊ ደህንነትንና ብሔራዊ ጥቅምን በሚመጥን ደረጃ ለማስጠበቅ ቁልፍ የሆነውን የባህር በር ጉዳይ መፍታት ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻ ከህዳሴው ጋር በተያያዘ የተገኘው ስኬት ሆነ ያለፍንባቸው ፈተናዎች ለሌሎች ማጋራት የድሉን አድማስ ያሰፋዋል፡፡ የህዳሴው ጉዞ ተመጋጋቢ የቴክኒክ እና የዲፕሎማቶች ቡድኖች በቅንጅት ከሰሩት ስራ አንጻር ሰፊ ልምድ የተገኘበት ነው፡፡ ሌላው ከህዳሴው የተማርነው መዘናጋት ዋጋ እንደሚያስከፍል ነው፡፡ ግድቡን እንደታሰበው በ5 ዓመት ባለማጠናቀቃችን ለዲፕሎማሲያዊ ጫና ከመዳረጋችን በተጨማሪ አገሪቱ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ አውጥታለች፡፡ ወደ 450 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ካሳ በስራው መቆምና በኮንታራክተሮች ያለመግባባት፣ ያለመናበብ ለተፈጠረው መጓተት ተከፍሏል፡፡ ስለዚህ የህዳሴውን ድል ሆነ ያሳለፍናቸውን ተግዳሮቶች ለሌሎች በተለይም ከአፍሪካዊያን መንገርና ማካፈል፣ አብረን የምናድግበት ሁኔታ እንዲፈጠር የድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡

እንዴት ታላቁን ስኬት ማጉላት እና ማስፋት እንችላለን?

የህዳሴውን ድል ማጉላት እና ማስፋት ካሉት ዘርፈ-ብዙ መነሻዎችና ጥቅሞች አንጻር እንዴት መከወን አለበት የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሊጠቀሱ የሚችሉ ዋና ዋና መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛ በአገር ውስጥ ለውጦችን ማካሄድና ማጠናከር ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የትርክት እና የአሰራር ለውጦችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሌሎች አገራት ትርክቶችን የሚደግፉ “ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት”፣ “የበቂ ዝናብ አገር ነን” የመሳሰሉ እሳቤዎችን ማረም አስፈላጊ ነው፡፡ በተያያዘ የፖሊሲዎች ትስስርን ማጠናከርና የውጭ ጉዳይ፣ የኃይል፣ የአካባቢ ለውጥ፣ ወዘተ ፖሊሲዎች ተመጋጋቢነት ማረጋገጥ ቁልፍ ነው፡፡

ሁለተኛ በተፋሰስ፣ በቀጠናዊ እና በአለም አቀፍ መድረኮች ንቁ ተሳትፎዎችን ማድረግና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ለንግግር፣ ለውይይት አምቢተኛ መሆን የለብንም፡፡ ነገር ግን በጥንቃቄና በብልጠት መሆን ያለበት ሲሆን ከአፍሪካ ማዕቀፍ ውጭ የሆነ የድርድር፣ የውይይት አማራጭ አለመቀበል እንዲሁም እንደ CFA ያሉ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ስምምነቶች እንዲከበሩና የንግግር መሰረት እንዲሆኑ ግልጽ አቋም መያዝ ተገቢ ነው፡፡ ሌላኛው እንደ UN Agenda 2030 እና AU Ageda 2063 ካሉ ቀጠናዊ እና አለም አቀፍ ማዕቀፎች ጋር ህዳሴው ያለውን ትስስር፣ መመጋገብ በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ ማሳየት አለብን፡፡ በዚህ ሂደት እንደ right to development፣ regional integration እና African solutions for African problems ያሉ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸውን መርህዎች መሰረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪ ግብጾች ኢትዮጵያን ለማሳጣት፣ ለማንቋሸሽ እንደሚያደርጉት በቃላት ንትርክ ውስጥ ባለመግባትና አንዳንድ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን ችላ በማለት ከአፍራሽና አሉታዊ አግባቦች የፀዳ ዲፕሎማሲ በመከተል በዲፕሎማሲው መስክ የተገኘውን ድል ይበልጥ ማጽናት ይቻላል፡፡

ሶስተኛ በተጠናከረ ሁኔታ ለግብጽ እንዲሁም ለሱዳን አጀንዳ ሰጪ ወደመሆን መሸጋገር አለብን፡፡ በዚህ ረገድ የግብጽን እና የሱዳንን አፍራሽ ብያኔና እንቅስቃሴ በሳይንሳዊ መንገድ ለመመከት የሚረዱ ዕድሎችን መፍጠር ይቻላል፡፡ ስለሆነም ለኮሚዩኒኬሽን ትኩረት መስጠት የሚያስፈልግ ሲሆን አለም አቀፍ ቋንቋዎችን መጠቀምና ራሳችንን በስፋት ለአለም መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በሱዳን እና በግብጽ ያሉ ግድቦች ምን ያህል በትነት ውሃ እያባከኑ እንደሆነ፣ የናይልን ውሃ ከተፋሰስ ውጭ መውሰድ የመሳሰሉ ተግባራት ምን ያህል የተፋሰሱን ዘላቂ ልማት እንደሚጎዳ አለም አቀፍ ሚዲያዎችን፣ ምሁራንን፣ ተቋማትን በመጠቀም ማስተጋባት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪ ሱዳንን ከግብጽ ለመለየት ስራዎች ሊሰሩ የሚገባ ሲሆን በሱዳን ያለውን የውስጥ ፖለቲካ አዝማሚያ መጠቀም እንዲሁም በሱዳናዊያን ምሁራን፣ የቀድሞ ፖለቲከኞች፣ ተቃዋሚዎች ዘንድ ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ ግድቡ ያለውን በጎ አመለካከት አጉልቶ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡

በመጨረሻ በአለም መድረክ አጋዥ አቅም ሊሆኑን የሚችሉ አገራትን በኃይል ስርጭት፣ መስኖን ጨምሮ በእርሻ ኢንቨስትመንት መሳብ አለብን፡፡ በተለይም ካላቸው አቅምና ስትራቴጂክ ፍላጎቶች አንጻር እንደ የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ ቱርክ፣ ሞሮኮ ያሉ አገራት ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ አሁን የአለም አቀፍ ስርዓቱ እያስተናገደ ካለው ተለዋዋጭ ጠባይ አንጻር ዕድሎችን መቃኘት የሚያስፈልግ ሲሆን ብሔራዊ ጥቅም-መር በሆነና ከውግንና በፀዳ መልኩ ወዳድነቶችን ማጠናከር፣ አዳዲስ ወዳጅነቶችን መመስረት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ውስጥ እንደ BRICS ላሉ የደቡብ-ደቡብ ትብብሮች የተመጣጠነ ትኩረት በመስጠት አገራዊ ውጥኖቻችን መተግበሪያ ተጨማሪ አስቻይ አቅም መፍጠር አለብን፡፡ በተጨማሪ የግድቡን ግንባታ ለመደገፍ ሲቸገሩ የነበሩ ባለ ብዙ ወገን ተቋማት እና አለም አቀፍ የፋይናንስ ድርቶች አሁን በኃል ስርጭት ሊሳተፉ የሚችሉበትን ሁኔታ ማጤን ተገቢ ነው፡፡

ማጠቃለያ፤

መጋቢት 2003 ዓ.ም መሰረት-ድንጋይ ሲጣል የተበሰረው የኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ዝምታ የመስበር ተግባራዊ ጉዞ ጳጉሜ 2017 ዓ.ም ግድቡ ተጠናቆ ሲመረቅ በድል ተቋጭቷል፡፡ ያለፉት አስራ አራት (14) የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዓመታት ብዙ ስኬቶች እንዲሁም ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶች ያስተናገዱ ናቸው፡፡ ህዳሴ እንደ አገር ከስኬቶቹም ከተግዳሮቶቹም ብዙ አስተምሮናል፡፡ ስለዚህ ድሉን በትልቅነቱ እያከበርንና የታለፈባቸውን መንገዶች እየዘከርን ዛሬን እና ነገን በሚመጥንና እንደ አገርና ህዝብ የምናማትረውን የብልዕግና ከፍታ በማሰብ ሩጫው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ መሰረታዊው ነገር አለም ተለዋዋጭ ነው፣ ሁኔታዎች ተለዋዋጭ ናቸው፡፡ ስለዚህ ድሉን እያጣጣምን፣ ለሁሉም ራሳችንን ማዘጋጀት፣ የበለጠ መስራት አለብን፡፡

About the author
Befikadu Birru is a researcher at the African Affairs Department in the Institute of Foreign Affairs.

Disclaimer:

The content disseminated by the Institute of Foreign Affairs (IFA) – including, but not limited to, publications, public statements, events, media appearances, and digital communications – reflects the views of individual contributors and does not necessarily represent the official positions or policies of the Institute, its partners, or any affiliated governmental or non-governmental entities.

While the IFA endeavors to ensure the accuracy, integrity, and timeliness of the information presented, it makes no representations or warranties, express or implied, regarding the completeness, reliability, or suitability of such content for any purpose. The Institute expressly disclaims any liability for errors or omissions, as well as for any actions taken or decisions made based on the information provided.

The inclusion of external links, references, or third-party resources does not constitute an endorsement by the Institute. Additionally, engagement on social media platforms – including, but not limited to, likes, shares, retweets (RTs), or reposts – shall not be interpreted as an endorsement or validation of the views expressed therein.

Readers and audiences are encouraged to exercise critical judgment and seek independent verification when interpreting or relying upon any information disseminated through publications and posts on the Institute’s platforms or representatives.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *