ወጣቶች በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያ ያላቸውን ክህሎት በማጎልበት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መትጋት አለባቸው – ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለፁ

‎**************

‎

‎የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ለአንድ ወር በዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያ ለወጣት ተማሪዎች በሰመር ካምፕ ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና አጠናቋል።

‎

‎በስልጠናው ማጠቃለያ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ የወደፊቷ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የለውጥ አስኳልና የልማቱ ዋነኛ መዘውር በሆኑት ወጣቶችዋ ትከሻ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

‎

‎ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም ለሀገር ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና በማዋል አይተኬ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

‎

‎በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያም ዘመኑን የዋጀና ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ክህሎት በመታጠቅና በየጊዜው ራሳቸውን በማብቃት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትጋት መስራት እንዳለባቸው ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል።

‎

‎ዲፕሎማሲ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ በዘርፉ ብቁና ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

‎

‎በዚህ ረገድ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በክረምት መርሐግብር በወጣቶች ላይ የጀመረው ተግባር አበረታች መሆኑን በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል።

‎

‎ኢንስቲትዩቱ በዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት የወጣቶችን ክህሎት ለማዳበር እየሰጠ ያለውን ስልጠና አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀው፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

‎

‎የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፤ ዲፕሎማሲ ሀገራችን የሰነቀችውን የብልፅግና ራዕይ ለማሳካት ቁልፍ ሚና ካላቸው ዘርፎች መካከል ግንባር ቀደም መሆኑን ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *